EBC (Ethiopian Broadcasting Corporation) is a 24 hour working public media.
Ethiopian Broadcasting Corporation is a national media which disseminates its news and programs world wide via Television, Radio and Internet.


EBC

ከንቲባ አዳነች አቤቤ 106 የቀበሌ ቤቶችን ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአገር ባለውለታዎች አስረከቡ
******************
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ 106 የቀበሌ ቤቶችን ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አቅመ ደካሞች፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአገር ባለውለታዎች ለሆኑ እና እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በመለየት በእጣ አስረክበዋል።
ከንቲባዋ "ከህዝብ ጋር ባደረግነው ውይይት የተሰጡንን ጥቆማዎችን ጭምር ተጠቅመን ባደረግነው ማጣራት የለየናቸውን ነዋሪዎቻችንን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ የተዘነጉ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አቅመ ደካማ ወገኖችን እንባ በማበስ እና ከነበሩበት አስከፊ ሕይወት በመታደግ ነገን በተስፋ እንዲያዩ የሚያስችል ስራ ተከናውኗል" ብለዋል።
በተለይም ከአራዳ ክፍለ ከተማ ከቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ ለተነሳችሁ፣ በሶስተኛ ወገን ክርክር ምክንያት ስትንገላቱ የቆያችሁ ዛሬ ችግሩን ፈተን የመኖሪ የቤት ስላገኛችሁ እጅግ ደስተኞች ነን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
#ኢትዮጵያታሸንፋለች #አዲስአበባ #Ethiopia #ebcdotstream

1 day ago | [YT] | 1,886

EBC

ኢትዮጵያ እና ሮማኒያ ያላቸውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ መከሩ
*******************
በቡካሬስት በተካሄደው የኢትዮጵያ-ሮማኒያ የንግድ ፎረም ላይ በስዊዘርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር እና በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው የተመራ ልዑካን ቡድን ተሳትፏል።
በፎረሙ ሮማኒያ ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያላችትን ትብብርን ለማስፋት ያላትን ፍላጎት CIB ፕሬዝዳንት ሚስተር ኢዩሊዩ ስቶክሎሳ ሮሳ አስታውቀዋል።
አምባሳደር ፀጋብ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም እድሎችን ለተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች፣ የተደረጉ ማሻሻያዎችን እና የኢትዮጵያን እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ አቅም አብራርተዋል።
በንግድ ፎረሙ ላይ ከሮማኒያ በኩል ፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድ ባለቤቶችን እና ባለሀብቶች ተሳታፊ ሲሆኑ በኢንቨስትመንት ማዕቀፎች፣ በዘርፉ ተስፋዎች እና እድሎች ዙሪያም ውይይት አድርገዋል።

1 day ago | [YT] | 234

EBC

አፈርን ወደ ማዕድንነት የሚቀይሩት ኮንታዎች
************

‎ኮንታ ዞን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ይገኛል። አካባቢው ያልተገለጠ እምቅ ሀብት ባለቤት ነው።

‎የመደመር መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አማካይነት የገለጠው የዝሆን ዳና ሎጅ ቱሪስቶችን እያስተናደ ይገኛል።

‎የኮንታ ሕዝብ የሚታወቅበት ሌላው ሀብቱ የችግር መፍቻ የሆነው ሀገር በቀል ዕውቀቱ ነው። በኮንታ አባቶች ለትውልድ ያስተላለፉት ዕውቀት ዛሬም ይተገበራል።

‎አፈርን ወደ ብረት ማዕድንነት የመቀየር ጥበብ በኮንታ ዞን፣ ኦሽካ ዴንቻ አካባቢ ነዋሪዎች ዘንድ በቀላሉ ይከወናል።

‎በኮንታዎች ዘንድ መሬት ውስጥ የብረት ማዕድን መኖር አለመኖሩን ለማወቅ በመጀመሪያ መሬቱ በእግር መታ መታ ይደረጋል፤ ከዚያም ጆሮን መሬት ላይ ለጥፎ በማድመጥ ማዕድን መኖር አለመኖሩ ይለያል።

ማዕድን መኖሩ ከታመነ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ይመርቁና ወንዶች የማዕድን ይዘት ያለው አፈር ቆፍረው ያወጣሉ።
‎በሴቶቹ በኩል ትልልቅ መቀቀያ ጋኖች ይዘጋጁና አፈሩን ወደ ጋኑ በመጨመር በዙሪያው ያለማቋረጥ እሳት በወናፍ በማንደድ አፈሩ ቀልጦ እስኪፈስ ድረስ ይቀቀላል።

‎በዚህ መሀል ታዲያ የሚበላና የሚጠጣው ተዘጋጅቶ የሚሠሩ ሰዎች በባህላዊ ሙዚቃ ጭምር እንዲነቃቁ እና እንዲበረቱ ይደረጋል።

‎በደንብ ከቀለጠ እና ከአፈሩ ከተለየ በኋላ በኋላ ብረት ማዕድኑ ላይ ውሃ ጨምሮ በማቀዝቀዝ በእርሻ መሣሪያ፣ የቤት ውስጥ መገልገያ እና ጌጣጌጥ መልክ ተበጅቶ ለሽያጭ ይቀርባል።

‎በአካባቢው በ4 ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ የብረት ማዕድን ስለመኖሩ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አበበ ደምሴ ይገልፃሉ።

‎ይህ ሀብት ጥልቅ ጥናት ተካሂዶበት የአካባቢውን ነዋሪ በስፋት ተጠቃሚ ማድረግ አለመቻሉን የሚያነሱት ኃላፊው፤ አልሚ ባለሀብቶች ቢሳተፉበት የተሻለ ውጤት ማግኘት ይቻላል ባይ ናቸው።

‎እስከአሁን የሚሠራበት ባህላዊው የማዕድን ማውጣት ጥበብ ‎በቴክኖሎጂ ቢታገዝ የመደመር መንግሥት ለማዕድን ሀብት ለሰጠው ትኩረት አጋዥ ሚና እንደሚኖረው እሙን ነው።

‎በሲሳይ ደበበ

1 day ago | [YT] | 275

EBC

የከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት
***********
በከተማችን እየተተገበሩ ካሉ የዜሮ ግብ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ተረጂነት እና ልመናን ዜሮ ማድረግ ነው።
ዛሬ ማለዳ በአዲስ ከተማ፣ በአቃቂ ቃሊቲ፣ በየካ እና በቂርቆስ ክፍለ ከተሞች፣ አራት G+4 የማምረቻ እና መሸጫ ህንፃዎችን ከዚህ ቀደም በምግብ ዋስትና (ሴፍቲኔት) ፕሮግራም ታቅፈው ሲሰሩ ለነበሩ የከተማችን ነዋሪዎች አስረክበናል።
የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች 976 አንቀሳቃሾች ሲሆኑ፣ በ292 ኢንተርፕራይዞች እንዲደራጁ ተደርጓል።
የከተማ አስተዳደራችን በሥራ ዕድል ፈጠራ፣ በማምረቻና መሸጫ ቦታ አቅርቦት፣ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ህይወት በመለወጥና ከድህነት በማውጣት ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት እንዲችሉ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
አስተዳደራችን ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከ520 ሺህ በላይ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎችን በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል በመፍጠር ከተረጂነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር ችሏል።
ውድ ተጠቃሚዎች፣ የተፈጠረላችሁን የስራ ዕድል በአግባቡ በመጠቀም ከተረጂነት ወደ አምራችነት በመሸጋገር በአጭር ጊዜ ውጤታማ ሆናችሁ ስላየን እጅግ ደስተኞች ነን።
ዛሬ ያስረከብናችሁ የመስሪያ ቦታ ነገ የእናንተ እህቶች፣ ወደፊትም ወንድሞችና ልጆች ተረክበው የሚሰሩበት መሆኑን ተገንዝባችሁ በኃላፊነት ልትጠቀሙበት ይገባል።
በቀጣይም በስልጠና ያገኛችሁትን ክህሎት በስራ ህይወታችሁ በመተግበር በርትታችሁ የበለጠ ውጤታማ በመሆን ሌሎችም የእናንተን መንገድ እንዲከተሉ ማድረግ ይጠበቅባችኋል።

1 day ago | [YT] | 502

EBC

‘ፋይዳ’ ለሌሎች ሀገሮች ያስገኘው ፋይዳ
*************************
በአውሮፓውያኑ 2024 በዓለም ዙሪያ 5 ቢሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ዲጂታል መታወቂያ እንደያዙ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ዜጎች ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ፍትሐዊ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ በርካታ ሀገራት የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ደኅንነቱ የተረጋገጠ ልዩ መለያ በማቅረብ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለማግኘት እንዲሁም የሰነዶች ማጭበርበርን ለመከላከል የሚረዳው ዲጂታል መታወቂያ ቀልጣፋ ሥርዓት በመገንባት ረገድ ያለው ዓለም አቀፍ ተጠቃሚነት ምን ይመስላል የሚለውን ጥቂት እንመልከት።
የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓትን በአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ (ፋይዳ)፣ ናይጄሪያ (ኤን አይ ኤን)፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ያሉ ሀገሮች የተሻለ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለመፍጠር ጥቅም ላይ እያዋሉት ይገኛሉ። ይህም ሥርዓቱ በአፍሪካ እየተስፋፋ መምጣቱን ያመላክታል።
ኢስቶኒያ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽነትን በቀዳሚነት በመምራት የምትታወቅ ነች። ‘ኢ አይ ዲ’ ተብሎ የሚጠራው የኢስቶኒያ ዲጂታል መታወቂያ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
ሙሉ መረጃውን ሊንክ ተጭነው ያንብቡ:- www.ebc.et/Home/NewsDetails?NewsId=3516

1 day ago | [YT] | 302

EBC

ፓስፖርት ማውጣት ዜጎች የሚቸገሩበት ጉዳይ እንዳይሆን በተቋማዊ ሪፎርሙ ተሠርቷል - የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት
************************
ተቋማዊ የአሠራር ዝማኔ ያደረገው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ፓስፖርት ማውጣት ዜጎች የሚቸገሩበት ጉዳይ እንዳይሆን መሥራቱን አስታውቋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ከኢቢሲ ዳጉ መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ከአሠራር ጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶች እና የሚነሡ ቅሬታዎችን ለመፍታት በትኩረት መሠራቱን ገልጸዋል።
በተለይም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የዜጎች የፓስፖርት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የአቅም ግንባታ ላይ ትኩረት ስለመሰጠቱ ነው የተናገሩት።
በዚህም ባለፈው የ2017 በጀት ዓመት ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ፓስፖርት መስጠት ስለመቻሉ ዋና ዳይሬክተሯ አመላክተዋል።
ይህን ቁጥር ከፍ ለማድረግ የተቋሙ ሠራተኞች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን እና አገልግሎቱ በ2 ፈረቃ መሰጠት መጀመሩን አስረድተዋል።
በዚህ የሚፈጠረውን አቅም በመጠቀም በተያዘው የ2018 በጀት ዓመት አራት ሚሊዮን ዜጎች ፓስፖርት እንዲያገኙ እየተሠራ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
ይህን እሙን በማድረግ ውስጥ በተለይም በተደረገ ተቋማዊ ጥናት አማካኝነት ብዛት ያላቸው ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጓዙበትን ርቀት በማጤን የቅርንጫፍ ማስፋፋት ስለመደረጉ ገልጸዋል።
ለአራት ሚሊዮን ዜጎች ተደራሽ ለመሆን የሚሠሩ መሠረተ ልማቶች፣ የሚፈጠረው ብቁ የሰው ኃይል እና የሚካብተው የአሠራር ልምድ ለቀጣዮቹ ጊዜያት ላለው አሠራር አቀጣጣይ እንደሚሆን ነው የተናገሩት።
አሁን ያለው የፓስፖርት ክፍያ ተመን የዜጎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ስለመሆኑም የተጠየቁት ዋና ዳይሬክተሯ፣ የዶክመንቱን ደኅንነት የሚያረጋግጥ ማይክሮ ቺፕ የተካተተበት እና የማይክሮ ቺፕ ቴክኖሎጂ ውድ እና ፓስፖርቱንም ለማተም በርካታ ደረጃዎችን የሚያልፍ እንደሆነ ጠቁመው፣ የወጣው ተመን ከሌሎች ሀገራት አንፃር ሲታይ ክፍያው ዝቅተኛ ስለመሆኑ አመላክተዋል።
በሀገር ውስጥ የዜጎች የመክፈል አቅም ሲቃኝም አስቻይ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
የኢ-ፓስፖርት አገልግሎት በ2017 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ስለመጀመሩ አስታውሰው፣ ያንን ተከትሎ በተሻሻለው ክፍያ በተለይም ፓስፖርቱ ዘመኑን የዋጀ እና ኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያን የሚገልጽ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል።
የክፍያ ሥርዓቱ አማራጮች ያሉት ሲሆን በ2 ወር ከ15 ቀን ለሚወሰድ ፓስፖርት 5 ሺህ ብር ሲከፈል፣ በአስቸኳይ አገልግሎት የ25 ሺህ ብር ክፍያ በ2 ቀን ፓስፖርት ማግኘት ይቻላል።

2 days ago | [YT] | 270

EBC

አየር መንገዱ 30ኛውን ቦይንግ ድሪምላይነር አውሮፕላን ተረከበ
*******
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አዲስ ቦይንግ 787- 8 ድሪምላይነር አውሮፕላን ዛሬ ተረክቧል፡፡
አየር መንገዱ የተረከበው አዲሱ አውሮፕላን በአንድ ጊዜ 213 መንገደኞችን ማጓጓዝ ያስችላል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱን አውሮፕላን መረከቡ፤ በባለቤትነት የያዛቸውን የቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖች ቁጥር 30 አድርሶታል፡፡
አየር መንገዱ አዲሱን አውሮፕላን መረከቡ፤ አፍሪካን ከዓለም በማገናኘት እየሰጠ ያለውን ምቹና ጥራት ያለው አገልግሎት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያስችለው ገልጿል፡፡
አዲሱ ቦይንግ 787- 8 ድሪምላይነር አውሮፕላን እጅግ ዘመናዊ ሲሆን፣ ከሌሎች አውሮፕላኖች አንፃር አነስተኛ የድምፅ ብክለት ያለውና ይበልጥ አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም አውሮፕላኑ ሰፊ የመስኮት እይታ ያለው በመሆኑ፤ መንገደኞች በረራ ሲያደርጉ የተሻለ ምቾት እንዲኖራቸው የሚረዳ መሆኑ ተገልጿል።

2 days ago | [YT] | 245

EBC

የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየታደሰ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ
********
ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ እንብርት የሚገኘውን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያንን የሕንጻ እድሳት ሥራ ጎብኝተናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ከዓድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ታሪክ አለው፤ በዚህም የተነሣ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ጊዜ እንደ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ ዋጋ ከፍሏል ብለዋል፡፡ በእሳት እስከ መቃጠልና ጥቁር ቀለም እስከ መቀባትም ደርሷል ሲሉም አቶ ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል።
ቤተ ክርስቲያኑ ደረጃውን በጠበቀና ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየታደሰ መሆኑን መመልከታቸውንም አስታውቀዋል።
የዓድዋ ሙዚየም በአካባቢው መገንባቱ፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ዐደባባይ ጥገና መደረጉ እና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ አካባቢው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከል እየሆነም ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
አሁን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያን ሕንጻና ግቢ ታሪካዊና ዘመናዊ በሆነ መንገድ መታደሱ ደግሞ፣ ታሪኩን የተሟላ እንዲሆን እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
የሕንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የጥበበ ዕድ እና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ አስደናቂ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ እና የአካባቢው ጥገና አሁን ከጀመርናቸው የከተማ ማዘመን ሥራዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ አደራ እላለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
#ebcdotstream #EBC #Ethiopia

2 days ago | [YT] | 265

EBC

የፀረ ሙስና ትግሉ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
********
ሙስናን የመከላከል ትግል መላው ማህበረሰብ ፣ ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊይዙት ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ዛሬ 22ኛውን ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀንን “ትውልድን በስነ-ምግባር፣ ተቋምን በአሰራር” በሚል መሪ ሀሳብ ስናከብር ሙስናን ለመዋጋት ያለንን ቁርጠኝነት እና የገባነውን ቃል በማደስ ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሙስናን የብልፅግናችን ፀር፣ የኢፍትሀዊነት ምንጭ በመሆኑ ብሔራዊ አጀንዳ አድርገን ያፋፋምነው ትግል ከዚህ ቀደም የነበረን አስከፊ መንግስታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት አስችሏል ሲሉም ገልጸዋል።
በዚህም እንደ ሀገር ብሎም እንደ ከተማ የህዝብና የመንግሥትን ሀብት በተገቢው የልማት ስራዎች ላይ በማዋላችን አስደናቂ የልማት ውጤቶች ማሳየት ችለናል ሲሉም ጠቁመዋል።
መንግሥታዊ/ስርዓታዊ የተደራጀ ሌብነትን ማስቀረት ብንችልም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚታይ በመንግስት ሃላፊዎች እና ሰራተኞች የሚፈፀመው ሌብነት እና ጉቦኝነት ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ በመሆኑ ለሙስና አጋላጭ አሰራሮችን ለመዝጋት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሙስናን ከምንጩ ለማድረቅ የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን በማጠናከር፣ መንግሥታዊ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆንና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን በተሟላ መልክ ለመከላከል የሁሉንም ተቋማት ትግል እና የሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል ብለዋል።
ቤተሰብ፣ ማኅበረሰቡ፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችም ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ በፀረ-ሙስና ትግል ውስጥ በአመለካከትም በተግባርም ሙስናን የሚጠየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር የማይተካ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመሆኑም የፀረ-ሙስና ትግላችን ይበልጡን ውጤታማ እንዲሆን የተጀመሩ የሪፎርም ተግባራትን ማጠናከር አስፈላጊ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።
#ebcdotstream #EBC #Corruption

2 days ago | [YT] | 168