ሄመን ዘተዋህዶ ቲዮብ

† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን †

† ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፩ †

=>አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ዐሥራ አንድ በዚች ቀን የግብጽ ደቡብ ከሆነ ከመጺል አውራጃ ከሬስ ከተማ ሰዎች ወገን የሆነ ቅዱስ አባት አባ በኪሞስ አረፈ።

እርሱም የአባቱን በጎች የሚጠብቅ ነበር ዕድሜውም ዐሥራ ሁለት ዓመት ሲሆነው ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ በጐልማሳ አምሳል ተገለጠለትና በአንድነት ሒደን እንመነኵስ ዘንድ ትሻለህ አለው እርሱም አዎን አለ ሁለቱም ተስማምተው ወደ አስቄጥስ ገዳም በአንድነት ተጓዙ ሦስት አረጋውያን መነኰሳትንም አገኙ አባ በኪሞስም ከእነርሱ ጋር ሃያ አራት ዓመታትን ኖረ።

ከዚህም በኋላ አባ በኪሞስ ከዚያ ተነሥቶ የሦስት ቀን ጐዳና ያህል ተጓዘና ሩቅ ወደ ሆነ በረሀ ውስጥ ገባ ሰይጣናትም በእሪያዎችና በዘንዶዎች አምሳል ሁነው መጡበት ሊነክሱትም አፋቸውን ከፍተው ከበቡት እርሱ ግን የአጋንንትን ሐሳብ አወቀ በእግዚአብሔርም ኃይል እፍ አለባቸው በዚያንም ጊዜ ተበተኑ።

እርሱም ወንዝ አገኘ ሰባት ሰባት ቀን እየጾመ በዚያ ሦስት ዓመት ኖረ በሱባዔውም መጨረሻ በመሀል እጁ ተምር መልቶ ያንን ይመገባል ውኃም በጥቂቱ ይጠጣል ሁለት ሽህ አራት መቶ ጊዜ በሌሊት እንዲሁም በቀን ሁለት ሽህ አራት መቶ ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን ይጸልያል።

ከዚህም በኋላ አርባ አርባ ቀን እየጾመ ሃያ አራት ዓመታት ያህል ኖረ አርባውም ቀን ሲፈጸም አንድ ጊዜ ይበላል ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ቆዳው ከዐጥንቶቹ ጋር እስቲጣበቅ ሰማንያ ቀን ጾመ በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ይበላና ይጠጣ ዘንድ እንጀራና ውኃን አመጣለት ያም ውኃና እንጀራ ሳያልቅ እስከ አረፈ ድረስ ብዙ ዓመታትን ኖረ።

ፈጣሪ እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ ተገልጦ ወደ አገሩ እንዲመለስ አዘዘው በዚያንም ጊዜ ተነሥቶ ሔደ ወደ አገሩም ደርሶ በዚያ ታናሽ ማደሪያ ጎጆ ሠርቶ በውስጡ ብቻውን የሚኖር ሆነ ወደርሱም ለሚመጣ ሁሉ መጠጊያና ወደብ በጎ አለኝታም ሆነ ሰዎችም ሁሉ በትምህርቱ እየተጽናኑ ኖሩ ንጹሕ በሆነ አምልኮቱ በትሩፋቱና በተጋድሎው መንፈሳዊ ቅናትን ይቀኑበት ነበር።

በአንዲት ዕለትም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ተሸክሞ ወደ ኤፍራጥስ ምድር አደረሰው የዚያ አገር ሰዎች በመተላለፍ ከእውነተኛ ሃይማኖት ወጥተው ነበርና ሁሉንም ወደ ቀናች ሃይማኖትና ወደ በጎ ምግባር መለሳቸው ከዚያም ወደ ቦታው ተመለሰ።

አንድ ጊዜም ሽጦ ምግቡን ያገኝ ዘንድ አገልግሎችን ተሸክሞ ወደ ከተማ ሲሔድ በጎዳና ላይ ደክሞት አገልግሎቹን አስቀምጦ ጥቂት ያርፍ ዘንድ ተቀመጠ በዚያንም ጊዜ ከአገልግሎቹ ጋር የእግዚአብሔር ኃይል ተሸክሞ ወደሚሻው ቦታ አደረሰው።

በዚያንም ወቅት አባ ሲኖዳ ከፍተኛ የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ በራእይ አየና ይህ ታላቅ ምሰሶ ምንድን ነው ብሎ ደነገጠ የእግዚአብሔርም መልአክ ተገልጦ ይህ አባ በኪሞስ ነው አለው። አባ ሲኖዳም ወዲያውኑ ተነሥቶ ወደ አባ በኪሞስ አገር እስቲደርስ በእግሩ ተጓዘ ከዚያችም ቀን በፊት ከቶ አላየውም ነበር በተገናኙም ጊዜ እርስበርሳቸው ሰላምታ ተሰጣጡ።

አባ በኪሞስም ወጥ ሊአበስል ወደደ አባ ሲኖዳንም ይቺን እንስራ ያዛትና ሔደህ ውኃ ቀድተህ መልተህ አምጣልኝ አለው በዚያንም ጊዜ አባ ሲኖዳ ተነሣና ያቺን እንስራ ተሸከማት ውኃውንም ቀድቶ መልቶ አመጣለት ወጡንም ፈልቶና በስሎ አገኘው በዚያንም ጊዜ አባ በኪሞስ መሆኑን አወቀ ከእርሱም ጋር ሰላምታን ደገመ እጅ በመነሣሣትም ሰላምታ ተለዋወጡ።

ከዚህም በኋላ አባ ሲኖዳ ስለርሱ ያየውን ራእይ ነገረው በእርሱም ዘንድ ጥቂት ቀኖች ኖረ።

ዳግመኛም በአንዲት ቀን በአንድነት ሲጓዝ የሞተ ሰው ራስ አገኙ አባ ሲኖዳም በበትሩ ነቅነቅ አደረገውና ምውት ሆይ ያየኸውን ትነግረንና ታስረዳን ዘንድ ተነሣ አለው በዚያን ጊዜ ነፍሱ ወደ ዐፅሙ ተመልሳ ሥጋ ለብሶ ተነሣና ሰገደላቸው በሲኦል የሚሠራውንም ሁሉ በየወገናቸውም በውስጧ የሚሠቃዩትን እርሱም አረማዊ እንደሆነ ነገራቸው። እንዲህም አለ ክብር ይግባውና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያመኑ ትእዛዙን ግን ያልጠበቁ በአሕዛብ ሥራና በአረማውያን ርኵስት የኖሩ ከእኛ በታች የሚኖሩ ክርስቲያኖች አሉ አለ ቅዱሳንም ተመልሰህ ተኛ አሉት ወዲያውኑ እንደ ቀድሞው ሆነ።

ከዚህም በኋላ አባ ሲኖዳ ቅዱስ በኪሞስን ተሰናብቶ ወደ ቦታው ተመለሰ። ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ቅዱስ አባ በኪሞስ አገልጋዩን ጠርቶ በኖረበት ቦታ ሥጋውን እንዲቀብር አዘዘው። ከዚህም በኋላ በሆድ ዝማ ሕመም ጥቂት ታመመ። ቅዱሳንን በአንድነት ወደርሱ ሲመጡ አያቸው በዚያንም ጊዜ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። መላእክትም ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከአደረሷት እያመሰገኑና እየዘመሩ አሳረጓት።

መላ ዕድሜውም ሰባ ዓመት ሆነ ዐሥራ ሁለት ዓመት በዓለም ውስጥ ሃምሳ ስምንት ዓመት በምንኵስና ሥራ ኖረ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
፨፨፨
አርኬ
ሰላም ለከ ፀዋሬ ክቡድ አስፈሬዳ። ወመንሥኤ ምውት በምድረ በዳ። ዐስበ ፃማከ በኪሞስ ወዘተቀንዮትከ ፍዳ። መንበረ ብርሃናዌ ወአክሊለ ክብር ፀዓዳ። እግዚአብሔር አርአዩ ለአባ ሲኖዳ።
፨፨፨

=>በዚችም ቀን የኤጲስቆጶሱ በርተሎሜዎስና የሰማዕቱ በጥላን መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
፨፨፨
አርኬ
ሰላም ለከ በርተሎሜዎስ አቡነ። ዘደለወከ በርትዕ ኤጲስቆጶሰ ከዊነ። እምጽድቅ ኲሉ ዘይጸንሐነ። ኃይለ ጸሎትከ ይዕቀብ ኪያነ። በአምሳለ ብንት ዘየዓቅብ ዐይነ።
ሰላም ለልደትከ ቴዎድሮስ ፍሡሐ ገጽ። አምሳለ ፍሬ ሥርናይ ወፍሬ ሠናይ ዕፅ። ውስተ ፍኖትከ ሚጠኒ እምነ ፍኖትየ ዘዳኅጽ። በእንተ ሥጋከ በዝብጠተ በትር ቅሩጽ። ወበእንተ ዐፅምከ ካዕበ በማኅረፅ ኅሩፅ።
፨፨፨

=>ታሕሳስ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ታላቁ አባ በኪሞስ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ
4.ቅዱስ በጥላን

=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
5.ቅድስት ሐና ቡርክት

=>+"+ በእሸቅድምድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ: ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ:: የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን:: +"+ (1ቆሮ. 9፥24)

፨፨፨

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶ።
( ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

1 day ago | [YT] | 691