ቀናንሞስ ሚዲያ - Qenanmos Media

የአእላፋትን ዝማሬ እንዴት እንተቸው?

የቢሆንና ትቸት ምልከታየ ነው ።ያላየሁትን ጨምሩበት

ከስሙ ብንነሳ እንኳን ዝማሬ የተገለጠው በአእላፋት አገልግሎት መሆኑን ያሳየናል ።የመጀመሪያወቹ አእላፋትም አመስግነው የማይደክሙ የሰማይ መላእክት ሲሆኑ ዝማሬም ጥንተ ሀገሩ ሰማይ ነው። የልደት ዕለት ደግሞ አእላፋት መላእክት ከሰው ልጆች ጋራ በጋራ ዘምረዋል። በብርሀን ተጥለቅለቀው በቤተልሔም በጋራ አመስግነዋል።

ባለፈው ዓመት በቦሌ መድኃኔዓለም የተመለከትነው የአእላፋትዝማሬም በጋራ መዘመርን በኅብረት ማመስገንን መሠረት ያደረገ መሰባሰብን የፈጠረ ድንቅ ተስፋ ያለው የዐውደምሕረት ጅማሬ ነው። መስቀል አደባባይ የሚሉም አሉ። እርሱ ግን በልደት ዋዜማ አይመችም።
የአእላፋት ዝማሬ አሠራሩን ማስፋት ያለበት ድንቅ ጅማሬ እንጅ በአጭሩ እንዲጨናገፍ የምንፈልገው መሆን የለበትም። በኔ እይታ መርሓግብሩ በውሱን ቦታና በውሱን ማኅበራት ሳይታጠር ሁሉምን ያሳተፈ የጋራ ዝግጅት ታክሎበት ሀገር አቀፍ የአእላፋት ዝማሬ ተጧጡፎ ከዚህ በላይ ሰፍቶ ማየት ትክክለኛ ትውልዱንና ቤተክርስቲያንን የማሥተሳሰር አንድ እርምጃ ነው።

ብዙዎቹ ወጣቶች የልደት ዋዜማን የሚያሳልፉት በአልባሌ ቦታዎች በኮንሰርት ዝግጅች በከፍተኛ መጠጥና በጭፈራ ቤት እንደነበር በዓላት በመጡ ቁጥር በየሚዲያው የሚሠራጩ ማስታወቂያዎች ራሳቸው ምሥክሮቻችን ናቸው።

መቸም መጠጥ ቤቶችና የጨፈራ ቦታቦች የልደት ኮንሰርት ሲያዘጋጁ የእስልማና (የፕሮቴስታንት)ወጣቶችን ታሳቢ በማድረግ አልነበረም።

አብዛኛው የነዚህ አስረሽ ምችው አድማቂ ወጣቶች እኛ የረሳናቸው በአግባቡ ያልሰበሰብናቸው የቤተክርስቲያን ልጆች ናቸውና።

የዛሬ ዓመት ከበዓል ማግሥት ያገኘሁት አንድ የራይድ ሹፌር የነገረኝን አስተማሪ ገጠመኝ ላካፍላችሁ።

አገልጋይ መሆኔን ነገሬው ጥቂት ከተነጋገርን በኋላ የአእላፋት ዝማሬ ሒደው ነበር በማለት ጠየቀኝ። እኔ አልሔድኩም አንትስ ? ሹፌሩ እንዲህ አለኝ ።አባዬ እኛማ ጉድ ሆንልዎት ከጋደኞቸ ጋራ እየጠጣን ነበር የምናመሸሸው ስለአእላፋት ዝማሬ ስንሰማ ከመዝሙሩ ተመልሰን እንጠጣለን ተባብለን ወደቦሌ መድኃኔዓለም ብናቀና በዚያው ሳንመለስ አደርን

ጓደኞቸም ሰዓቱ ስለሔደ መጠጥ ቤት ከዚህ በኋላ አንሔድም አሉኝ። ድሮ ባለቤቴ ስትደውል ሠክሬ ነበር ስልክ የማነሳላት በዚያ ሌሊት ቤተክርስቲያን መሆኔን ስነግራት ግን ማመን አቃታት።

የልደት ዕለትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሳንጣላ በደስታ አከበርን በማለት የመለወጥ ጅማሬውን አካፈልኝ።

የአእላፋት ዝማሬ ለካስ የምእመናን መያዣ መረብ መሆን ጀምሯል ።በመጠጥ በጭፈራ በሱስ በጥርጣሬ የተያዙትን ከተከማቹበት የመጥፋት ባሕር እየመዘዘ የሚያጠምዳቸው ሁኗል ።በማለት ውስጤ በጣም ተደሰተ።

በእውነት የአእላፋት ዝማሬን ማቃናት ማድነቅና ማረም እንጅ ማክስምን የሚያስከትል ትችት መሰንዘር እንደማይገባን ተገነዘብኩ። የገዳማትን ጉዞ ያስቀርብናል የሚል ስጋት ያደረባቸው ቀናዎችም ትችቱን ተጋርተውት ተመልክቻለው።

በኔ ምልከታ ግን እንኳን የላሊበላን ጉዞ ሊያሰናክል ይቅርና የአእላፋት ዝማሬ የጉዞ አገልግሎት የሚያጠናክር በሕግ የታቀፈ አስተባባሪ ቢኖርና መርሓ ግብሩ ሀገር አቀፍ ቢሆን ይሔ የተሰበሰበ ወጣትም ዓቅሙ የፈቀደለት ሁሉየሚሳተፍበት የጉዞ አገልግሎትን እያሰፋ ይሔዳል እንጅ እየታረመ እየተገመገመ የሚዘረጋ መስመር ከተፈጠረለት በፍጹም መሰናክል የሚሆንበት አጋጣሚ አይታየኝም።

ወጣቱ ከሰዓታት ዝማሬ ባለፈ ሥጋውን ደሙን መቀበል እንዲችል ማድረግና ከበዓላት ዝግጅት ወደሕይወት ዝግጅት ማሸጋገር ደግሞ ከመርሓ ግብሩ አዘጋጆች የሚጠበቅ ከባድ የቤት ሥራ ቢሆንም።ለጊዜውም ከሐጢአት ጎዳና ነጥቆ ይኽን ሁሉ ወጣት እውነተኛ ቤቱ ውስጥ መደበቅ በራሱ እጅግ የሚደነቅ ደግሞም የሚወደድ ዋጋም የሚያሰጥ አገልግሎት ነው።

ነገርግን
ጎልተው መታረም ይኖርባቸዋል ብየ የማስባቸውንው ለመግለጽ
1በየቦታው የሚታረዱ የሚሳደዱ ክርስቲያኖችን በጸሎት በማሰብና ጠንካራ የአንድነትና የትብብር ጥሪ ማበድረግ መጠናቀቅ መቻል አለበት እንጅ የሠርገኛ ስብስብ ብቻ መምሰል የለበትም ብ

2ዓውደምሕረቱን ወደቲያትርነት እየለወጥነው እስኪመስል ድረስ በዓለማዊ ሥራቸው አንቱ የተባሉ ግለሰቦችን የነፍስ አርዓያ አስመስለን ከምእመንነት ያለፈ ማስታወቂያ ለንስሓ የማያበቃ ተአብዮን የሚያስከትል ገጽታ ግምባታ ማድረግ ጉዳቱ ስለሚከፋ መስተካከል ይኖርበታል።

3ዝማሬው የመላዋ ቤተክርስቲያን ሁኖ ሳለ በማኅበር ብቻ የታጠረ የባለቤትነት እንቅስቃሴ ስክነትና ግራቀኝ ምልከታ የሚያስፈልገው መሆኑን ማስገንዘብ ያስፈልጋል።

4የሚመረጡ የዓውደምሕረት መዝሙራት በመጠኑ የተሻሉ የዜማና የግጥም ሥርዓት ያላቸው እንዲሆኑና ሁሉን ለማስደሰት በማሰብ ቤተክርስቲያንን እንዳንጎዳ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

5ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ያነሷቸውን በጎ እርማቾች በመቀበል የሚስተካከሉ ነገሮችን ሁሉ በቀናነት በማስተካከል ቤተክርስቲያንን ማዕከል ያደረገ ቋሚ የመሰባሰቢያ መንገድ እንዲሆን የድርሻችን ማገዝ ይኖርብናል።

6የወጣቶቹን በመንፈሳዊ ስሜት መሰባሰብና በተስፋ መገኘታቸውን ተጠቅሞ ሌሎችን ለማጥቃት የሚደረጉ የሐሳብ የቃልና የተግባር እንቅስቃሴዎች ተፈጥረው ሌላ የመከፋፈል አደጋ እንዳያስከትሉ መጠንቀቅ ብቻ ሳይሆን ተባብሮ መሥራት ሐሳብን ማጋራት የጋራ ማድረግ በዕጅጉ ያስፈልጋል።

ከዚህ በተረፈ ለቤተክርስቲያናችን ከልክ በላይ ዋጋ እየከፈልን ስለዶግማ ለቀኖናዋና ለሥርዓቷና ከልብ እየተቆረቆርን ነገር ግን ሁሉንም በመርገም ሁሉን በመተቸት የምንጠመድ ከሆነ የቤክርስቲያኗን በጎ መዓዛ ማራኪ ማንነት እየሸፈንን ምሬትን ብቻ እያስተማርን ትውልዱ ከሩቅ ተስፋ ቆርጦ እንዲቀር እያደረግን ከሆነ የነገ ጸጸት እንዳይሆንበት ማበርታት ማገዝ ማረም መመረቅን ጎን ለጎን ማስኬት ይኖርብናል።
ቸሩ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንን ከፈተና ሕዝቡን ከመከራ ይጠብቅልን አሜን።

2 days ago | [YT] | 41